Thursday, July 5, 2018

✔ በአሏህ ስም እጅግ በጣም አዛኝና ሩህሩህ በሆነው እጀምራለሁ፡፡
الحمد لله وصلاة وسلام على رسول الله وعلى آله وصحبه ومن والاه ..... أما بعد

° በዚህ አጠር ያለ ትምህርት ስለ ሶብር(ትዕግስት) እንመለከታለን፡፡ በመጀመርያ ትዕግስት ምን ማለት ነው ? ሶብር በሸሪዐችን ምን አይነት ቦታ ተሰጥቶታል?
° ሶብር (ትእግስት) ማለት ፦ ኢማም ኢብንል ቀይም (አሏህ ይዘንለት) እንዲህ ገልፆታል...

አቡል ዐባስ እንዲህ ብሏል " ትዕግስት ማለት ነፍስን ከምትጠላው ነገር ማገድ ነው፡፡ አንደበትን ስሞታ ከማሰማት ማቀብ ነው፡፡ ሐዘንን ችሎ መሸከም ነው ትዕግስት ማለት፡፡ (ከመቸገር በኋላም) መጨረሻው ነፃ መውጣትን መጠበቅ ነው ትእግስት ፥ "

[ ጦሪቅ አልሂጅረተይን ፡ 338]

° ይህ ማለት በየትኛው የህይወታችን ክፍል ለሚያጋጥሙን የተለያዩ ችግሮች ፥ መበደሎች ፥ ሐዘን ፥ የመሳሰሉት ከነ ችግራቸው በመሸከም ከጀርባቸውን የሚጠብቀንን ፍሬ በማሰብ መቻልን ያጠቃለለ ትርጓሜ ነው፡፡

° ሶብር (ትእግስት) የኀይማኖት ግማሹ ክፌል ነው ይባላል፡፡ ኢማን ሁለት ግማሽ ክፍሎች አሉት፡፡ አንዱ ግማሽ ሶብር ፥ ሌላኛው ደግሞ ማመስገን (ሹክር) ነው፡፡ አሏህ እንዲህ ብሏል...
ٍ ۚ إِنَّ فِى ذَٰلِكَ لَـَٔايَٰتٍۢ لِّكُلِّ صَبَّارٍۢ شَكُورٍۢ

" በዚህ ውስጥ በጣም ታጋሽና አመስጋኝ ለሆነ ሁሉ መገሰጫዎች አሉበት፡፡" ሰበእ፡ 19

° የአሏህ ነብይ ሰለሏሁ አለይሒ ወሰለም እንዲህ ብለዋል ፦ ነፍሴ በእጁ በሆነችው ጌታ እምላለሁ አሏህ ለአንድ ሙእሚን አንድ ነገር አይፈፅምለትም ለርሱ መልካም ቢሆንለት እንጂ ፡፡ ደስታ የሚሰጥ ነገር ቢገጥመው ያመሰግናል ለርሱም መልካም ይሆንለታል፡፡ መጥፎም ነገር ቢገጥመው ትዕግስት ያደርጋል በዚህ መልካም ይሆንለታል፡፡ ይህ ለሙእሚን እንጂ የሚሀቀን ነገር አይደለም፡፡ "

[ ሙስሊም የዘገቡት እና ኢማም አህመድ]

° አንድ የአሏህ ባርያ በእለት እለት ስራዎቹ ፥ በዒባዳው ፥ በሚሠራቸው ዱንያዊ ተግባራት ፥ ዕውቀት ለመፈለግ በሚሄደው መንገድ ፥ ቤተሰብ ለማስተዳደር ሲሰራ በርካታ ነገሮች ይገጥሙታል፡፡ ይህን ጊዜ የሙእሚን ባህሪይ ደህና ነገር ሲያገኝ አሏህን ማመስገን ፥ መጥፎ ነገር ሲያገኘው በዚያ ላይ ትዕግስት በማድረግ ማሳለፍ ይጠበቅበታል፡፡

° ኢማም ኢብን አልቀይም ፦ እንደሚገልፁት የኢማን ደረጃ ሁሉንም በትዕግስትና በማመስገን ላይ የቆመ ነው... ይላሉ፡፡ ቀጥለውም ይህ ነገር ይበልጥ የሚያብራራው....

° አንድ ባርያ ወይ በፀጋ ውስጥ ወይም ደግሞ በችግር ውስጥ ከመሆን በጭራሽ አያገልም፡፡ በጸጋ ውስጥ ሆኖ ከሆነ ትዕግስትና ማመስገን ግድ ይለዋል፡፡ ማመስገን የተባለው (ለፀጋው) መፅናትና መቀመጥ እንዲሁም ቢጤዋንም ለማስጨመር ነው፡፡ ነገር ግን ትእግስት(በፀጋ ላይ) ይህን ነገር ከሚያስወግድብን ነገሮች መታገስ ነው፡፡ ፀጋችን የሚጠብቅልን ነገር በመሥራት ላይ መገኘት፡፡ ይህ ደግሞ ትእግስት የሚፈልግ ነው፡፡

° እዚህ ጋር ሐብታም ሆኖ አመስጋኝና ፥ ድሃ ሆኖ የታገሰ ሚስጥሩ ይታወቃል፡፡ ሁለቱንም ወደ ሶብርና ወደ ማመስገን ፈላጊዎች ናቸው (ያስፈልጋቸዋል)፡፡ አንዳንዴ የሃብታሙ ትእግስት ከድሃው ትእግስት የተሻለ ሊሆን ይችላል፡፡

° ማመስገን ትእግስትን የሚያሲዝ ነገር ነው ያለሱ የተሟላ አይሆንም፡፡ ትእግስትም ለማመስገን የሚያሲዝ ነገር ነው፡፡ ያለ እሱ የተሟላ አይሆንም፡፡ በማንኛውም ማመስገን የተወገደ ጊዜ ትእግስትም አብሮ ይወገዳል፡፡ ትዕግስትም ሲጠፋ ማመስገን አብሮ ይጠፋል፡፡

° አሏህ በባርያዎች ላይ በፀጋ ጊዜ እንደሚያመልኩት ሁሉ በችግርም ጊዜ ሊያመልኩት ይገባል፡፡

° ትእግስት 3 ደረጃዎች ይኖሩታል፡፡
1). በወንጀል ላይ መታገስ እንዳይተገብር...
2). በመታዘዝ ላይ መታገስ (ትእዛዙ እስኪፈፅም)
3). በችግር ላይ መታገስ (ወደ ጌታው ስሞታ እንዳያቀርብ)

° አንድ ባርያ ከነዚህ ሶስቱ አንዱ እንኳን ቢኖረው ሶብር በጭራሽ ከርሱ የሚወጣ ነገር አይደለም፡፡

° ትዕግስት አሏህ በቁርአን በ90 ቦታዎች ላይ ጠቅሶታል፡፡ አንዳንዴ (በትዕግስት) እያዘዘ ፥ አንዳንዴ የትዕግስት ባለቤቶች እያወደሰ ፥ አንዳንዴ ነብዩ (ሰለሏሁ አለይሒ ወሰለም) የሶብር ባለቤቶችን እንዲያበስሩ እያዘዘ ፥ አንዳንዴ የመብቃቃትና የድል መሥፈርት ሲያደርገው ፥ አንዳንዴ እርሱ አሏህ ከሶብር ባለቤቶች ጋር መሆኑ ሲገልፅ ፥ በትእግስትም ከአለማት የተመረጡትን ነብያትና ሩሱሎችን ሲያወድስበት ፥ (በተለያዩ ቦታዎች ጠቅሷል)፡፡

ስለ አሏህ ነብይ አዩብ (ዐሰ) አሏህ እንዲህ ብሏል...

وَخُذْ بِيَدِكَ ضِغْثًۭا فَٱضْرِب بِّهِۦ وَلَا تَحْنَثْ ۗ إِنَّا وَجَدْنَٰهُ صَابِرًۭا ۚ نِّعْمَ ٱلْعَبْدُ ۖ إِنَّهُۥٓ أَوَّابٌۭ

«በእጅህም ጭብጥ አርጩሜን ያዝ፡፡ በእርሱም (ሚስትህን) ምታ፡፡ ማላህንም አታፍርስ» (አልነው)፡፡ እኛ ታጋሸ ኾኖ አገኘነው፡፡ ምን ያምር ባሪያ እርሱ በጣም መላሳ ነው፡፡" ሷድ ፡ 44

° የነብያትና የሩሱሎች መደምደሚያ ለሆኑት እንዲህ ብሏል ፦

فَٱصْبِرْ كَمَا صَبَرَ أُو۟لُوا۟ ٱلْعَزْمِ مِنَ ٱلرُّسُلِ

" ከመልክተኞችም የቆራጥነት ባለቤቶች የኾኑት እንደ ታገሱ ሁሉ ታገስ፡፡ " አህቃፍ ፡35
° ስለ ነብዩሏህ ዩሱፍ (አሰ) አሏህ እንዲህ ብሏል ...

قَالُوٓا۟ أَءِنَّكَ لَأَنتَ يُوسُفُ ۖ قَالَ أَنَا۠ يُوسُفُ وَهَٰذَآ أَخِى ۖ قَدْ مَنَّ ٱللَّهُ عَلَيْنَآ ۖ إِنَّهُۥ مَن يَتَّقِ وَيَصْبِرْ فَإِنَّ ٱللَّهَ لَا يُضِيعُ أَجْرَ ٱلْمُحْسِنِينَ

«አንተ በእርግጥ አንተ ዩሱፍ ነህን» አሉት፡፡ «እኔ ዩሱፍ ነኝ፡፡ ይህም ወንድሜ ነው፡፡ አላህ በኛ ላይ በእርግጥ ለገሰልን፡፡ እነሆ! የሚጠነቀቅና የሚታገስ ሰው (አላህ ይክሰዋል)፡፡ አላህ የበጎ አድራጊዎችን ዋጋ አያጠፋምና» አለ፡፡ " (ዩሱፍ፡90)

° ይህ የሚያመለክተው ሶብር ከትልልቅ የኢማን ጉዳዮች እንደሆነ እንረዳለን፡፡ ልናዳብረውም ከሚገባን የህይወታችን ቅመሞች ሶብር አንዱና ዋነኛው ነው፡፡ በሌላ መልዕክት እንገናኛለን፡፡

ወቢላሒ አት-ተውፊቅ ....

© አቡ ሙስሊም ቢን ዐብድልሃሊም
.... ሸዋል 1439

No comments:

Post a Comment

የኢብኑ ተይሚያህ አቋም በተሃኩም ላይ...

  ፨ በአሏህ ሥም እጅግ በጣም አዛኝና በጣም ሩህሩህ በሆነው እጀምራለሁ፡፡ ፨ በዚህ ፅሁፍ ሼይኹል ኢሥላም ኢብኑ ተይሚያህን ከኸዋሪጆች አመለካከት እናጠራለን፡፡ አቡ ኢምራን ብዙዎች እንደምታውቁት ሁለት ገሪብ የኸዋሪጆችን...